የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ዜና መዋዕል 1

1
ሰሎሞን ጥበብ እንዲሰጠው ጠየቀ
1፥2-13 ተጓ ምብ – 3፥4-15
1፥14-17 ተጓ ምብ – 1ነገ 10፥26-292ዜና 9፥25-28
1አምላኩ እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበር፣ እጅግም ስላገነነው፣ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በመንግሥቱ ላይ ተደላድሎ ተቀመጠ።
2ከዚያም ሰሎሞን ለመላው እስራኤል፣ ለሻለቆች፣ ለመቶ አለቆች፣ ለዳኞች፣ ለእስራኤል መሪዎች ሁሉ እንዲሁም ለየቤተ ሰቡ አለቆች ተናገረ። 3እግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የአምላክ የመገናኛ ድንኳን በዚያ ስለ ነበር፣ ሰሎሞንና መላው ጉባኤ በገባዖን ወዳለው ኰረብታ ሄዱ። 4በዚያ ጊዜ ዳዊት የአምላክን ታቦት ከቂርያትይዓይሪም በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎ ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር፤ 5ይሁን እንጂ የሑር ልጅ፣ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው መሠዊያ በገባዖን በእግዚአብሔር ማደሪያ ድንኳን ፊት ለፊት ይገኝ ነበር፤ ስለዚህ ሰሎሞንና ጉባኤው ይህንኑ ፈለጉ። 6ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጥቶ በላዩ ላይ አንድ ሺሕ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።
7በዚያ ሌሊት እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገልጦ፣ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ሁሉ ጠይቀኝ” አለው።
8ሰሎሞን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ለአባቴ ለዳዊት ታላቅ ቸርነትን አሳይተኸዋል፤ እኔንም በእግሩ ተክተህ አንግሠኸኛል። 9አሁን እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ያነገሥኸኝ ብዛቱ እንደ ምድር ትቢያ በሆነ ሕዝብ ላይ ስለ ሆነ፣ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው ተስፋ ይጽና። 10ይህን ሕዝብ ለመምራት እንድችል፣ ጥበብና ዕውቀትን ስጠኝ፤ አለዚያማ፣ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊያስተዳድር ይችላል?”
11እግዚአብሔርም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “የልብህ መሻት ይህ ስለ ሆነ፣ ብልጽግናና ሀብት ወይም የጠላቶችህን ነፍስ ወይም ረዥም ዕድሜ ስላልጠየቅህ፣ ነገር ግን ባነገሥሁህ ሕዝቤ ላይ የምትገዛበትን ጥበብና ዕውቀት ስለ ጠየቅህ፣ 12ጥበብና ዕውቀት ይሰጥሃል፤ እንዲሁም ከአንተ በፊት የነበረ ማንኛውም ንጉሥ ያላገኘውን፣ ከአንተ በኋላም የሚነሣው የማያገኘውን ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር እሰጥሃለሁ።”
13ሰሎሞንም የመገናኛው ድንኳን ካለበት ከገባዖን ኰረብታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ።
14ሰሎሞን ሠረገሎችንና#1፥14 ወይም ሠረገለኞች ተብሎ መተርጐም ይችላል። ፈረሶችን ሰበሰበ፤ እርሱም አንድ ሺሕ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች ነበሩት፤ እነርሱንም በሠረገላ ከተሞችና ንጉሡ ባለበት በኢየሩሳሌም ከተማ አኖራቸው። 15ንጉሡ በኢየሩሳሌም ብሩንና ወርቁን እንደ ማንኛውም ድንጋይ፣ የዝግባውንም ዕንጨት ብዛት በየኰረብታው ግርጌ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው። 16የሰሎሞን ፈረሶች የመጡት ከግብጽና ከቀዌ#1፥16 ምናልባት ኪልቂያ ናት። ሲሆን፣ ከቀዌ የገዟቸውም የንጉሡ ነጋዴዎች ነበሩ። 17ከግብጽ ያስመጧቸውም አንዱን ሠረገላ በስድስት መቶ ሰቅል#1፥17 6.9 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ብር፣ አንዱን ፈረስ በአንድ መቶ ዐምሳ ሰቅል#1፥17 1.7 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ብር ገዝተው ነው። እነዚህንም ደግሞ ለኬጢያውያንና ለሶርያውያን ነገሥታት ሁሉ ይሸጡላቸው ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ