1 ጢሞቴዎስ 5
5
ስለ መበለቶች፣ ስለ ሽማግሌዎችና ስለ ባሪያዎች የተሰጠ ምክር
1አረጋዊውን ሰው እንደ አባትህ ቈጥረህ ምከረው እንጂ በኀይለ ቃል አትናገረው። ወጣት ወንዶችን እንደ ወንድሞች ተቀበላቸው፤ 2እንዲሁም አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና አስተናግዳቸው።
3በርግጥ ችግረኛ የሆኑትን መበለቶች ተንከባከባቸው። 4አንዲት መበለት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሯት፣ እነዚህ ልጆች የራሳቸውን ቤተ ሰብ በመርዳትና ለወላጆቻቸውም ብድራትን በመመለስ ከሁሉ በፊት እምነታቸውን በተግባር ለማሳየት መማር ይገባቸዋል፤ ይህ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነውና። 5በርግጥ መበለት የሆነች፣ ብቻዋንም የምትኖር ተስፋዋን በእግዚአብሔር ላይ ታደርጋለች፤ ለጸሎትና የእግዚአብሔርን ርዳታ ለመለመን ሌሊትና ቀን ትተጋለች። 6ምድራዊ ደስታን የምትሻዋ መበለት ግን በሕይወት ብትኖርም የሞተች ናት። 7ማንም የሚነቀፍበት ነገር እንዳይኖር፣ ይህንም ትእዛዝ ለሕዝቡ ስጥ። 8አንድ ሰው ዘመዶቹን፣ በተለይም የቅርብ ቤተ ሰቡን የማይረዳ ከሆነ ሃይማኖቱን የካደ፣ ከማያምንም ሰው ይልቅ የባሰ ክፉ ነው።
9ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት ያነሰ መበለት በመዝገብ ላይ አትጻፍ፤ ደግሞም የአንድ ባል ሚስት የነበረች#5፥9 ወይም ለባሏ ታማኝ የነበረች ልትሆን ይገባል፤ 10ልጆችን በማሳደግ፣ እንግዶችን በመቀበል፣ የቅዱሳንን እግር በማጠብ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና ለበጎ ምግባር ሁሉ ራሷን በመስጠት በመልካም ሥራም የተመሰከረላት መሆን አለባት።
11ወጣት መበለቶችን ግን እንዲህ ባለው መዝገብ አትጻፋቸው፤ ምክንያቱም ሥጋዊ ፍላጎታቸው ለክርስቶስ በገቡት ቃል ላይ በሚያይልበት ጊዜ ለማግባት ይሻሉና። 12በዚህም ፍርድን በራሳቸው ላይ ያመጣሉ፤ በመጀመሪያ የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና። 13በተጨማሪም ሥራ መፍታትንና ከቤት ቤት መዞርን ይለምዳሉ፤ ሥራ ፈት መሆን ብቻ ሳይሆን፣ የማይገባውን እየተናገሩ ሐሜተኞችና በሰው ጕዳይም ጣልቃ የሚገቡ ይሆናሉ። 14ስለዚህ ባል የሞተባቸው ወጣት ሴቶች እንዲያገቡ፣ ልጆች እንዲወልዱ፣ ቤታቸውን እንዲያስተዳድሩ፣ ጠላትም የሚነቅፍባቸውን ነገር እንዳያገኝ እመክራለሁ። 15በርግጥ ከዚህ በፊት አንዳንዶቹ ሰይጣንን ለመከተል ዘወር ብለዋል።
16አማኝ የሆነች ማንኛዋም ሴት በቤተ ሰቧ ውስጥ መበለቶች ቢኖሯት፣ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ መበለቶችን ብቻ መርዳት እንድትችል እርሷው ትርዳቸው እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ሸክም እንዲሆኑ አትተዋቸው።
17ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ የሚያስተዳድሩ፣ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚተጉ ሽማግሌዎች ዕጥፍ ክብር ይገባቸዋል፤ 18መጽሐፍም፣ “እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሰር፤#5፥18 ዘዳ 25፥4” ደግሞም፣ “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል#5፥18 ሉቃ 10፥7” ይላልና። 19በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ካልተደገፈ በቀር በሽማግሌ ላይ የሚቀርብ ክስ አትቀበል። 20ሌሎች አይተው እንዲጠነቀቁ ኀጢአት የሚሠሩትን በጉባኤ ፊት ገሥጻቸው።
21በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በተመረጡትም መላእክት ፊት እነዚህን ትእዛዞች ያለ አድልዎ እንድትጠብቅና አንዳችም ነገር በማበላለጥ እንዳታደርግ ዐደራ እልሃለሁ።
22በማንም ላይ እጅ ለመጫን አትቸኵል፤ ከሌሎችም ጋር በኀጢአት አትተባበር፤ ራስህን በንጽሕና ጠብቅ።
23ለሆድህና ደጋግሞ ለሚነሣብህ ሕመም፣ ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣበት እንጂ ከእንግዲህ ውሃ ብቻ አትጠጣ።
24የአንዳንድ ሰዎች ኀጢአት ግልጽ ነው፤ ከእነርሱም ቀድሞ ፍርድ ቦታ ይደርሳል፤ ሌሎችን ግን ኀጢአታቸው ይከተላቸዋል። 25መልካም ሥራም እንደዚሁ ግልጽ ነው፤ ግልጽ ያልሆነ ቢኖርም እንኳ ተሰውሮ አይቀርም።
Currently Selected:
1 ጢሞቴዎስ 5: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.