የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ጢሞቴዎስ 1

1
1በአዳኛችን በእግዚአብሔር፣ ተስፋችንም በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ትእዛዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፤
2በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለጢሞቴዎስ፤
ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት፣ ሰላምም ይሁን።
ከሐሰተኛ የሕግ መምህራን ስለ መጠበቅ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
3ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ ዐደራ እንዳልሁህ፣ አንዳንድ ሰዎች ከእንግዲህ የሐሰት ትምህርት እንዳያስተምሩ ታዝዛቸው ዘንድ በዚያው በኤፌሶን ተቀመጥ፤ 4ደግሞም ለተረትና መጨረሻ ለሌለው የትውልዶች ታሪክ ራሳቸውን አሳልፈው እንዳይሰጡ እዘዛቸው። እነዚህ ነገሮች በእምነት ከሆነው ከእግዚአብሔር ሥራ ይልቅ ክርክርን ያነሣሣሉ። 5የዚህ ትእዛዝ ዐላማ ግን ከንጹሕ ልብ፣ ከበጎ ኅሊና እንዲሁም ከእውነተኛ እምነት የሚገኝ ፍቅር ነው። 6አንዳንዶች ከእነዚህ ነገሮች ዘወር ብለው ወደ ከንቱ ንግግር ተመልሰዋል። 7የሕግ መምህራን ለመሆን ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ስለሚናገሩት ወይም አስረግጠው ስለሚሟገቱለት ነገር አያውቁም።
8ነገር ግን ሰው በአግባቡ ከተጠቀመበት፣ ሕግ መልካም መሆኑን እናውቃለን። 9ደግሞም ሕግ#1፥9 ወይም ሕጉ የተሰጠው ለጻድቃን ሳይሆን፣ ለሕግ ተላላፊዎችና ለዐመፀኞች፣ ፈሪሀ እግዚአብሔር ለሌላቸውና ለኀጢአተኞች፣ ቅድስና ለሌላቸውና እግዚአብሔርን ለሚንቁ፣ አባትና እናታቸውን ለሚገድሉ፣ ለነፍሰ ገዳዮች መሆኑን እናውቃለን፤ 10እንዲሁም ለዘማውያን፣ ከወንድ ጋር ለሚተኙ ወንዶች፣ ሰውን ለሚሸጡና ለሚገዙ፣ ለውሸተኞች፣ በሐሰት ለሚምሉ፣ ጤናማ የሆነውን ትምህርት ለሚፃረሩ ሁሉ ነው። 11ይህ ጤናማ ትምህርት ቡሩክ የሆነው እግዚአብሔር ለእኔ በዐደራ ከሰጠኝ የክብር ወንጌል ጋር የሚስማማ ነው።
ለጳውሎስ የተሰጠው የጌታ ጸጋ
12በአገልግሎቱ በመሾም ታማኝ አድርጎ የቈጠረኝን፣ ብርታትም የሰጠኝን ጌታችንን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ። 13ምንም እንኳ ከዚህ በፊት ተሳዳቢ፣ አሳዳጅና ዐመፀኛ የነበርሁ ብሆንም፣ ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረት ተደርጎልኛል፤ 14በክርስቶስ ኢየሱስ ከሆኑት እምነትና ፍቅር ጋርም የጌታችን ጸጋ ተትረፈረፈልኝ።
15“ክርስቶስ ኢየሱስ ኀጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ” የሚለው ቃል እውነተኛና ሰው ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ ነው፤ ከኀጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ። 16ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በእርሱ ለሚያምኑና የዘላለምን ሕይወት ለሚቀበሉ ወሰን የሌለው ትዕግሥቱን ከኀጢአተኞች ዋና በሆንሁት በእኔ እንደ ምሳሌ አድርጎ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ። 17እንግዲህ ዘላለማዊ ለሆነው፣ ለማይሞተው፣ ለማይታየውና ብቻውን አምላክ ለሆነው ንጉሥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብርና ምስጋና ይሁን፤ አሜን።
18ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ፤ አስቀድሞ ስለ አንተ በተነገረው ትንቢት መሠረት ይህን ትእዛዝ እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም እርሱን በመከተል መልካሙን ገድል እንድትጋደል ነው። 19እምነትና በጎ ኅሊናም ይኑርህ፤ አንዳንዶች ኅሊናቸውን ጥለው ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደሚጠፋ መርከብ እምነታቸውን አጥፍተዋል። 20ከእነርሱም መካከል እንዳይሳደቡ ትምህርት ያገኙ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፌ የሰጠኋቸው ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ይገኛሉ።

Currently Selected:

1 ጢሞቴዎስ 1: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ