የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ሳሙኤል 15:12-26

1 ሳሙኤል 15:12-26 NASV

ሳሙኤልም ጧት ተነሥቶ በማለዳ ሳኦልን ለመገናኘት ሄደ፤ ነገር ግን፣ “ሳኦል ወደ ቀርሜሎስ ሄዷል፤ ለራሱ ክብር የመታሰቢያ ሐውልት በዚያ ካቆመ በኋላ ተመልሶ ወደ ጌልገላ ወርዷል” ተብሎ ተነገረው። ሳሙኤል ባገኘው ጊዜ ሳኦል፣ “እግዚአብሔር ይባርክህ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ” አለው። ሳሙኤል ግን፣ “ታዲያ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ። ሳኦልም፣ “ሰራዊቱ ከአማሌቃውያን ማርከው ያመጧቸው ናቸው፤ ምርጥ ምርጦቹ በጎችና በሬዎች ለእግዚአብሔር ለአምላክህ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳይገድሉ የተዉአቸው ናቸው፤ የቀሩትን ግን በሙሉ አጥፍተናል” ብሎ መለሰ። ሳሙኤልም ሳኦልን፣ “ስማ! ትናንት ማታ እግዚአብሔር የነገረኝን ልንገርህ?” አለው። ሳኦልም፣ “ንገረኝ” ሲል መለሰለት። ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “በዐይንህ ፊት ታናሽ የነበርህ ብትሆንም፣ የእስራኤል ነገዶች መሪ ሆነህ የለምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቀብቶ አንግሦሃል። እግዚአብሔርም፣ ‘ሄደህ እነዚያን ኀጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ጨርሰህ እስክታጠፋቸውም ድረስ ውጋቸው’ ብሎ ልኮህ ነበር። ታዲያ እግዚአብሔርን ለምን አልታዘዝህም? ለምርኮውስ ተስገብግበህ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ለምን አደረግህ?” ሳኦልም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔርን ታዝዣለሁ፤ እግዚአብሔር በላከኝ መሠረት ሄጃለሁ፤ አማሌቃውያንን በሙሉ አጥፍቼ ንጉሣቸውን አጋግን አምጥቻለሁ። ሰራዊቱ ግን ከምርኮው ለእግዚአብሔር ከተለዩት መካከል፣ ምርጥ ምርጡን በግና በሬ፣ በጌልገላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ ወስደዋል።” ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣ በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል። ዐመፅ እንደ ጥንቈላ ያለ ኀጢአት፣ እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው። አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቅህ፣ እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።” ከዚያም ሳኦል ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን መመሪያ ጥሻለሁ፤ ሕዝቡን ፈርቼ ስለ ነበር፣ የጠየቁኝን ታዝዣለሁ። አሁንም፣ ኀጢአቴን ይቅር እንድትለኝ፣ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ አብረኸኝ እንድትመለስ እለምንሃለሁ።” ሳሙኤል ግን፣ “ከአንተ ጋር አልመለስም፤ አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃል፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል” አለው።