1 ነገሥት 7:1-37

1 ነገሥት 7:1-37 NASV

ሰሎሞን የራሱን ቤተ መንግሥት ሠርቶ ለመጨረስ ዐሥራ ሦስት ዓመት ፈጀበት። የሊባኖስ ዱር የተባለ ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ይህም ርዝመቱ መቶ ክንድ፣ ወርዱ ዐምሳ ክንድ፣ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ ሲሆን፣ በአራት ረድፍ የቆሙ የዝግባ ምሰሶዎች ደግፈው የያዟቸው አግዳሚ የዝግባ ተሸካሚዎች ነበሩት። ቤቱ ከምሰሶዎቹ ላይ ያረፉ አግዳሚ ተሸካሚዎች አሉት፤ በእያንዳንዱ ዐምድ ላይ ዐሥራ ዐምስት፣ በድምሩ አርባ ዐምስት ተሸጋጋሪዎች ሲኖሩ፣ ከእነዚህም ተሸጋጋሪዎች በላይ ከዝግባ የተሠራ የጣሪያ ክዳን ነበር። መስኮቶቹም ከፍ ብለው የተሠሩ በሦስት ምድብ የተከፈሉና ትይዩ ነበሩ። በሮቹ በሙሉ ባለአራት ማእዘን መቃኖች ያሏቸው፣ በሦስት ምድብ የተከፈሉና ትይዩ ነበሩ። ሰሎሞን፣ “ባለብዙ ምሰሶ አዳራሽ” የተባለ ቤት ሠራ፤ የዚህም ርዝመቱ ዐምሳ ክንድ፣ ወርዱ ሠላሳ ክንድ፣ ነበር፤ በስተ ፊት በኩልም ጣራ ያለውና በአዕማድ የተደገፈ መመላለሻ ነበረው። ዳኝነት የሚያይበትንም የዙፋን ችሎት አዳራሽ ሠራ፤ ይኸውም የፍትሕ አዳራሽ የተባለው ነው፤ ይህንም ከወለሉ አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ ሳንቃ ሸፈነው። ከአዳራሹ በስተጀርባ ባለው አደባባይ መኖሪያው እንዲሆን የተሠራው ቤተ መንግሥትም የዚሁ ተመሳሳይ ነበር። ሰሎሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ይህንኑ ቤተ መንግሥት የመሰለ አዳራሽ ሠራ። ከውጭ አንሥቶ እስከ ትልቁ አደባባይ፣ ከመሠረቱ አንሥቶ እስከ ድምድማቱ ያለው የሕንጻ ሥራ በሙሉ፣ በውስጥም በውጭም በልክ በልኩ በተቈረጠና አምሮ በተጠረበ ምርጥ ድንጋይ የተሠራ ነበር። መሠረቱም ዐሥርና ስምንት ክንድ ርዝመት ባላቸውና ምርጥ በሆኑ ታላላቅ ድንጋዮች የተሠራ ነበር። በላዩም ላይ ምርጥ የሆኑ፣ በልክ በልኩ የተቈረጡ ድንጋዮችና የዝግባ ሳንቃዎች ነበሩ። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ ከመመላለሻ በረንዳው ጭምር እንደ ትልቁ አደባባይ አምሮ በተጠረበ ሦስት ረድፍ ድንጋይና ተስተካክሎ በተከረከመ በአንድ ረድፍ የዝግባ ሳንቃ የታጠረ ነበር። ንጉሥ ሰሎሞንም መልእክተኛ ልኮ ኪራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ አስመጣ፤ የኪራም እናት ከንፍታሌም ነገድ ስትሆን፣ እርሷም መበለት ነበረች፤ አባቱ የጢሮስ ሰው ሲሆን፣ የናስ ሥራ ባለሙያ ነበር። ኪራም በማናቸውም የናስ ሥራ ጥበብን፣ ማስተዋልንና ዕውቀትን የተሞላ ሰው ነበር፤ እርሱም ወደ ንጉሥ ሰሎሞን መጥቶ የተመደበለትን ሥራ ሁሉ አከናወነ። ኪራም የእያንዳንዱ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ፣ ዙሪያው ዐሥራ ሁለት ክንድ የሆነ፣ ሁለት የናስ ምሰሶዎች ሠራ። እንዲሁም በምሰሶዎቹ ዐናት ላይ የሚሆኑ፣ ሁለት ጕልላት ከቀለጠ ናስ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ጕልላት ቁመት ዐምስት ክንድ ነበር። በምሰሶዎቹ ዐናት ላይ ላሉት ጕልላቶችም ጌጥ እንዲሆኑ፣ ለእያንዳንዳቸው ሰባት የመረብ ሰንሰለት አበጀ፤ ደግሞም በምሰሶዎቹ ላይ ያሉትን ጕልላቶች ለማስጌጥ የእያንዳንዱን መረብ ዙሪያ የሚከብቡ ሮማኖች በሁለት ረድፍ ሠራ፤ ለሁለቱም ጕልላቶች ያደረገው ተመሳሳይ ነበር። በመመላለሻው ምሰሶዎች ዐናት ላይ ያሉት ጕልላቶች ቁመታቸው አራት ክንድ ሲሆን፣ የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው። በሁለቱም የምሰሶ ጕልላቶችና ከመርበቡ ቀጥሎ ባለው የክብ ቅርጽ ላይ ዙሪያውን በሙሉ ሁለት መቶ ሮማኖች በተርታ ነበሩ። ዐምዶቹንም በቤተ መቅደሱ መመላለሻ ላይ አቆመ፤ በስተ ደቡብ ያቆመውን ዐምድ “ያኪን”፣ በስተሰሜን በኩል ያለውንም “ቦዔዝ” ብሎ ጠራው። ዐናቱ ላይ ያሉት ጕልላቶች የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው። የምሰሶዎቹም ሥራ በዚህ ሁኔታ ተፈጸመ። ቅርጹ ክብ፣ ስፋቱ ከጠርዝ እስከ ጠርዝ ዐሥር ክንድ፣ ቁመቱ ዐምስት ክንድ የሆነ ክብ ገንዳ ከቀለጠ ብረት ሠራ፤ ዙሪያውም ሲለካ ሠላሳ ክንድ ሆነ። ከገንዳው ከንፈር በታችም፣ በእያንዳንዱ ክንድ ላይ እንደ ቅል ያሉ ዐሥር ቅርጾች ዙሪያውን በሁለት ረድፍ ከብበውታል፤ እነዚህም ከገንዳው ጋራ አንድ ወጥ ሆነው በሁለት ረድፍ ተሠርተው ነበር። ገንዳውም፣ ሦስቱ ፊታቸውን ወደ ሰሜን፣ ሦስቱ ወደ ደቡብ፣ ሦስቱ ወደ ምዕራብ፣ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ባዞሩ የዐሥራ ሁለት በሬዎች ምስሎች ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ገንዳው በላያቸው ሆኖ የሁሉም የኋላ አካል በመካከል ላይ የገጠመ ነበር። የገንዳው ውፍረት አንድ ስንዝር ሲሆን፣ የከንፈሩ ጠርዝ ደግሞ የአበባ ቅርጽ ያለው የጽዋ ከንፈር የመሰለ ነው፤ ይህም ሁለት ሺሕ የባዶስ መስፈሪያ ያህል ውሃ የሚይዝ ነበር። እንዲሁም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ዐሥር ባለመንኰራኵር የዕቃ ማስቀመጫዎች ከመዳብ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ርዝመት አራት ክንድ፣ ወርድ አራት ክንድ፣ ቁመትም ሦስት ክንድ ነበር። የዕቃ ማስቀመጫዎቹ የተሠሩት እንደዚህ ነው፤ እነዚህም ቀጥ ብለው ከቆሙ ደጋፊዎች ጋራ የተያያዙ ባለአራት ማእዘን ጠፍጣፋ ናሶች ነበሯቸው። ዳርና ዳር ባሉት ድጋፎች መካከል በሚገኙት ጠፍጣፋ ናሶች ላይ የአንበሶችን፣ የኰርማዎችንና የኪሩቤልን ምስል አደረገ፤ በድጋፎቹም ላይ እንደዚሁ አደረገ። ከአንበሶቹና ከኰርማዎቹ በላይና በታች በኩል ደግሞ የአበባ ጕንጕን የሚመስሉ ተቀጥቅጠው የተሠሩ ቅርጾች ነበሩ። እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት የናስ መንኰራኵርና መንኰራኵሮቹ የሚሽከረከሩባቸው የናስ ወስከምቶች እንዲሁም እያንዳንዳቸው በአራቱም ማእዘን ገጽ ላይ የአበባ ጕንጕን ቀልጦ የተሠራባቸው የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበረው። በዕቃ ማስቀመጫዎቹም ውስጥ ጥልቀቱ አንድ ክንድ የሆነ ባለክብ ክፍተት ነበር፤ ይህም ክፍተት ድቡልቡል ሆኖ ከታች ከመቆሚያው በኩል ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ወርድ ሲኖረው፣ በክፍተቱም ዙሪያ ቅርጾች ነበሩ፤ ክፈፎቹ ግን ባለአራት ማእዘን እንጂ ክብ አልነበሩም። አራቱ መንኰራኵሮች በዕቃ ማስቀመጫው ጠፍጣፋ ናስ ሥር ሲሆኑ፣ የመንኰራኵሮቹ ወስከምቶች ደግሞ ከዕቃ ማስቀመጫዎቹ ጋራ የተያያዙ ነበሩ፤ የእያንዳንዱም መንኰራኵር ስፋት አንድ ክንድ ተኩል ነበር። መንኰራኵሮቹ የሠረገላ መንኰራኵር መሰል ሲሆኑ፣ ወስከምቶቹ የመንኰራኵሮቹ ክፈፎችና ዐቃፊዎቻቸው እንዲሁም ወስከምቶቹ የሚገቡባቸው ቧንቧዎች በሙሉ ከቀለጠ ብረት የተሠሩ ነበሩ። እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት ወጣ ያለ እጀታ ነበረው። በዕቃ ማስቀመጫው ጫፍ ላይ ግማሽ ክንድ የሆነ ዙሪያ ክብ ነበረበት፤ ድጋፎቹና ጠፍጣፋ ናሶቹ ከዕቃ ማስቀመጫው ዐናት ጋራ የተያያዙ ነበሩ። እርሱም በድጋፎቹና በጠፍጣፋ ናሶቹ ላይ ባለው ቦታ ሁሉ፣ ዙሪያውን የአበባ ጕንጕን እያደረገ ኪሩቤልን፣ አንበሶችንና የዘንባባ ዛፎችን ቀረጸ። ዐሥሩም የዕቃ ተሸካሚዎች የተሠሩት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ሁሉም ከአንድ ቅርጽ ቀልጠው የወጡ ስለ ሆነ፣ በመጠንና በቅርጽ ፍጹም ተመሳሳይ ነበሩ።