የይሁዳና የእስራኤል ሕዝቦች ብዛታቸው እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ሆነ፤ ይበሉ፣ ይጠጡና ይደሰቱም ነበር። ሰሎሞንም ከወንዙ አንሥቶ እስከ ፍልስጥኤማውያን ምድር፣ ከዚያም እስከ ግብፅ ዳርቻ ያሉትን መንግሥታት ሁሉ ገዛ፤ እነዚህም አገሮች ግብር አመጡለት፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ተገዙለት። ለሰሎሞን በየቀኑ የሚገባለትም ቀለብ ይህ ነበር፤ ሠላሳ ኮር ማለፊያ ዱቄት፣ ስድሳ ኮር መናኛ ዱቄት፣ ዐሥር ቅልብ ሰንጋዎች፣ ሃያ ግጦሽ መሬት ላይ የሚውሉ በሬዎች፣ መቶ በግና ፍየል እንዲሁም ዋሊያ፣ ሚዳቋ፣ የበረሓ ፍየልና ምርጥ አዕዋፍ። ከወንዙ በስተ ምዕራብ፣ ከቲፍሳ እስከ ጋዛ ያሉትን መንግሥታት ስለ ገዛ፣ በሁሉም አቅጣጫ ሰላም ሆኖለት ነበር። በሰሎሞን ዘመን ሁሉ ከዳን አንሥቶ እስከ ቤርሳቤህ ያለው ይሁዳና እስራኤል፣ እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ ጥላ ሥር በሰላም ለመኖር በቃ። ሰሎሞን ሠረገላ የሚጐትቱ ፈረሶች የሚያድሩበት አራት ሺሕ ጋጣና ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች ነበሩት። የየአውራጃው ሹማምትም በየወር ተራቸው ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ማእድ የሚቀርቡትን ሁሉ ምንም ሳያጓድሉ ይቀልቡ ነበር፤ እንዲሁም ለሠረገላ ፈረሶችና ለፈጣን ፈረሶች የተመደበውን ገብስና ጭድ ከተፈለገው ቦታ ድረስ ያመጡ ነበር። አምላክ ለሰሎሞን ጥበብንና እጅግ ታላቅ ማስተዋልን እንዲሁም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋትን ሰጠው። የሰሎሞን ጥበብ ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብ በጣም የላቀ ከግብፅም ጥበብ ሁሉ የበለጠ ነበር፤ እርሱም ከማንም ሰው ይልቅ ጥበበኛ ነበር፣ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታን፣ ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ደግሞም ከደራል ይልቅ ጥበበኛ ነበር፤ ዝናውም በዙሪያው ባሉት አሕዛብ ሁሉ ተሰማ። እርሱም ሦስት ሺሕ ምሳሌዎችን ተናገረ፤ የመሓልዩም ቍጥር ሺሕ አምስት ነበር። ከሊባኖስ ዝግባ አንሥቶ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው ሂሶጵ ስለ ዕፀዋት ተናግሯል፤ እንዲሁም ስለ እንስሳት፣ ስለ ወፎች፣ በሆዳቸው ስለሚሳቡ እንስሳትና ስለ ዓሦችም ተናግሯል፤ ጥበቡን ከሰሙት ከዓለም ነገሥታት ሁሉ የተላኩ፣ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለማድመጥ መጡ።
1 ነገሥት 4 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ነገሥት 4
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ነገሥት 4:20-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos