1 ነገሥት 14
14
አኪያ በኢዮርብዓም ላይ የተናገረው ትንቢት
1በዚያ ጊዜ የኢዮርብዓም ልጅ አብያ ታመመ፤ 2ኢዮርብዓም ሚስቱን እንዲህ አላት፤ “ተነሺ፣ የኢዮርብዓም ሚስት መሆንሽ እንዳይታወቅብሽ ሆነሽ፣ ወደ ሴሎ ሂጂ፤ በዚህ ሕዝብ ላይ እንደምነግሥ የነገረኝ ነቢይ አኪያ እነሆ፤ በዚያ ይገኛል። 3ስትሄጂም ዐሥር እንጀራ፣ ጥቂት ሙልሙል ዳቦ እና አንድ እንስራ ማር ይዘሽ ሂጂ፤ እርሱም በልጁ ላይ የሚደርሰውን ይነግርሻል።” 4ስለዚህ የኢዮርብዓም ሚስት ያላትን አድርጋ በሴሎ ወደሚገኘው ወደ አኪያ ቤት ሄደች።
በዚህ ጊዜ አኪያ ከማርጀቱ የተነሣ ዐይኖቹ ፈዝዘው ነበር። 5እግዚአብሔር ግን ለአኪያ፣ “እነሆ፤ የኢዮርብዓም ሚስት ስለ ታመመው ልጇ ልትጠይቅህ ሌላ ሴት መስላ ትመጣለችና እንዲህ ብለህ መልሳት” ብሎ ነገረው።
6አኪያም የእግሯን ኮቴ ድምፅ እበሩ ላይ እንደ ሰማ እንዲህ አላት፤ “የኢዮርብዓም ሚስት ሆይ ግቢ፤ ግን ለምንድን ነው ሌላ ሴት መስለሽ ለመታየት የፈለግሽው? ለአንቺ ከባድ ነገር እንድነግርሽ ተልኬአለሁ። 7አሁንም ሂጂና ኢዮርብዓምን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው ብለሽ ንገሪው፤ ‘ከሕዝቡ መካከል አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤ 8ከዳዊት ቤት መንግሥቱን ቀድጄ ለአንተ ሰጠሁህ፤ አንተ ግን በፊቴ መልካም ነገር በማድረግ ብቻ ትእዛዜን እንደ ጠበቀው፣ በፍጹም ልቡም እንደ ተከተለኝ እንደ ባሪያዬ እንደ ዳዊት አልሆንህም። 9ከአንተ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ አንተ የከፋ ሥራ ሠራህ፤ ለራስህም ከቀለጠ ብረት ሌሎች አማልክትን ሠራህ፤ ቍጣዬን አነሣሣህ፤ ወደ ኋላህም ጣልኸኝ።
10“ ‘ስለዚህ እኔም በኢዮርብዓም ቤት ላይ ጥፋትን አመጣለሁ፤ ባሪያም ይሁን ነጻ ዜጋ የኢዮርብዓምን ወንድ ልጅ ሁሉ ከእስራኤል አስወግዳለሁ፤ ኩበትም ዐመድ እስኪሆን ድረስ እንደሚቃጠል፣ እኔም የኢዮርብዓምን ቤት እንዲሁ አቃጥላለሁ። 11ከኢዮርብዓም ወገን በከተማ የሞተውን ውሾች፣ በባላገር የሞተውን ደግሞ የሰማይ አሞሮች ይበሉታል፤ እግዚአብሔር ተናግሯልና!’
12“እንግዲህ አንቺም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ የምትኖሪበትን ከተማ እግርሽ እንደ ረገጠ፣ ልጁ ይሞታል፤ 13እስራኤልም ሁሉ አልቅሰው ይቀብሩታል። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከኢዮርብዓም ቤት ሁሉ መልካም ነገር ያገኘበት እርሱ ብቻ ስለ ሆነ፣ በወግ በማዕርግ የሚቀበር እርሱ ብቻ ነው።
14“ከዚህም በላይ፣ እግዚአብሔር የኢዮርብዓምን ቤተ ሰብ የሚያስወግድ ንጉሥ በእስራኤል ላይ ለራሱ ያስነሣል፤ ይህም ዛሬ፣ አሁኑኑ ይሆናል።#14፥14 በዕብራይስጡ የዚህ ዐረፍተ ነገር ትርጕም በትክክል አይታወቅም። 15እግዚአብሔር እስራኤልን በውሃ ውስጥ እንደሚንቀጠቀጥ ሸንበቆ ያንቀጠቅጠዋል፤ የአሼራን ምስል ዐምድ#14፥15 በዚህም ሆነ በሌሎቹም የመጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ክፍሎች፣ የአሼራ ጣዖት አምላክ ምስል ነው። በመሥራት እግዚአብሔርን ለቍጣ ያነሣሡት ስለ ሆነ፣ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላቸዋል፤ ከወንዙም ማዶ#14፥15 የኤፍራጥስ ወንዝ ነው። ይበትናቸዋል። 16ኢዮርብዓም ኀጢአት ሠርቶ፣ እስራኤልንም እንዲሠሩ በማድረጉ፣ እግዚአብሔር እስራኤልን ይተዋቸዋል።”
17የኢዮርብዓም ሚስትም ተነሥታ ወደ ቴርሳ ሄደች፤ የቤቱን መድረክ ወዲያው እንደ ተራመደች ልጁ ሞተ፤ 18ከዚያም ቀበሩት፤ እግዚአብሔር በባሪያው በአኪያ አማካይነት እንደ ተናገረ፣ እስራኤል ሁሉ አለቀሱለት።
19የቀረው የኢዮርብዓም ታሪክ፣ ያደረገው ጦርነትና አገዛዙም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፏል። 20ኢዮርብዓምም ሃያ ሁለት ዓመት ነግሦ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ ናዳብም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ ሮብዓም
14፥21፤ 14፥25-31 ተጓ ምብ – 2ዜና 12፥9-16
21የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ እርሱም እግዚአብሔር ስሙን በዚያ ለማኖር ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀምጦም ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ። እናቱም ናዓማ የተባለች አሞናዊት ነበረች።
22ይሁዳ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ከአባቶቻቸው ይልቅ እነርሱ በሠሩት ኀጢአት ይበልጥ የቅናት ቍጣውን አነሣሡ፤ 23እንዲሁም በእያንዳንዱ ኰረብታና በየትልልቁ ዛፍ ጥላ ሥር የማምለኪያ ኰረብቶችን አዕማደ ጣዖታት፣ የአሼራን ምስል ዐምድ ለራሳቸው አቆሙ። 24ከዚያም ይልቅ፣ የቤተ ጣዖት ወንደቃዎች በምድሪቱ ላይ ነበሩ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳድዶ ያስወጣቸው አሕዛብ የፈጸሙትን አስጸያፊ ድርጊት ሁሉ እነዚህም ፈጸሙ።
25ሮብዓም በነገሠ በዐምስተኛው ዓመት፣ የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ 26የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ንብረትና የቤተ መንግሥቱን ንብረት ዘርፎ ወሰደ፤ ሰሎሞን ያሠራው የወርቅ ጋሻ፤ ሰሎሞን ያሠራቸው የወርቅ ጋሻዎች ሁሉ እንኳ ሳይቀሩ ሁሉንም ነገር አጋዘ። 27ስለዚህ ንጉሥ ሮብዓም እነዚህን ለመተካት ሲል፣ የናስ ጋሻዎች ሠርቶ የቤተ መንግሥቱን ቅጥር በር ለሚጠብቁ የዘብ አለቆች በኀላፊነት ሰጠ። 28ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ፣ ዘቦቹ ጋሻዎቹን አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ከዚያም በዘብ ጥበቃው ክፍል መልሰው ያስቀምጡ ነበር።
29የቀረው የሮብዓም አገዛዝ፣ ያደረገውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 30በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር። 31ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በዳዊት ከተማ ተቀበረ። እናቱ ናዓማ የተባለች አሞናዊት ነበረች። ልጁ አብያም#14፥31 አንዳንድ የዕብራይስጥና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ከዚህ ጋራ ይስማማሉ (2ዜና 12፥16 ይመ)፤ አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ትርጕሞች ግን፣ አቢያም ይላሉ። በርሱ ፈንታ ነገሠ።
Currently Selected:
1 ነገሥት 14: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.