1 ነገሥት 10
10
ንግሥተ ሳባ ሰሎሞንን እንደ ጐበኘች
10፥1-13 ተጓ ምብ – 2ዜና 9፥1-12
1የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ዝና እና ከእግዚአብሔር ስም ጋራ ያለውን ግንኙነት በሰማች ጊዜ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች ልትፈትነው መጣች። 2ታላቅ አጀብ አስከትላ ሽቱ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮችን በግመሎች አስጭና ኢየሩሳሌም ከደረሰች በኋላ፣ ወደ ሰሎሞን ገብታ በልቧ ያለውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት። 3ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ መለሰላት፤ ከንጉሡ የተሰወረና ሊመልስላት ያልቻለው አንድም ጥያቄ አልነበረም። 4የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፣ የሠራውንም ቤተ መንግሥት ስትመለከት 5እንዲሁም በገበታው ላይ የሚቀርበውን መብል፣ የሹማምቱን አቀማመጥ፣ የአስተናባሪዎቹን አቋቋምና የደንብ ልብሳቸውን፣ ጠጅ አሳላፊዎቹን፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያቀረባቸውን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች#10፥5 ወይም ወደ ላይ የሚወጣባቸው ደረጃዎች ተብሎ መተርጐም ይችላል። ባየች ጊዜ እጅግ ተደነቀች።
6ንጉሡንም እንዲህ አለችው፤ “ስለ ተናገርሃቸው ነገሮችና#10፥6 ወይም ስላከናወንሃቸው ነገሮች ወይም ስላገኘሃቸው ስኬቶች ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት እውነት ነው፤ 7ይሁን እንጂ፣ መጥቼ እነዚህን ነገሮች በዐይኔ እስካይ ድረስ የተነገረኝን አላመንሁም ነበር፤ በርግጥ ግማሹ እንኳ አልተነገረኝም፤ ጥበብህና ብልጽግናህ ከሰማሁት እጅግ ይልቃል። 8ሰዎችህ እንዴት ብፁዓን ናቸው! ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙ ሹማምትህ ምንኛ ብፁዓን ናቸው! 9በአንተ ደስ ተሰኝቶ በእስራኤል ዙፋን ላይ ያስቀመጠህ እግዚአብሔር አምላክህ ቡሩክ ይሁን፤ እግዚአብሔር በዘላለም ፍቅሩም እስራኤልን ከመውደዱ የተነሣ፣ ፍትሕና ጽድቅ እንዲሰፍን አንተን ንጉሥ አደረገህ።”
10ከዚያም ለንጉሡ አንድ መቶ ሃያ መክሊት#10፥10 4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ቅመማ ቅመሞችና የከበሩ ድንጋዮች ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰሎሞን ያበረከተችለትን ያን ያህል ብዛት ያለው ቅመማ ቅመም ከዚያ በኋላ ከቶ አልመጣም።
11ከኦፊር ወርቅ ያመጡት የኪራም መርከቦች፣ እጅግ ብዙ የሰንደል ዕንጨትና#10፥11 በዚህና በቍጥር 12 ላይ፣ የአልጉም ዕንጨት ከሚባለው ጋራ ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። የከበሩ ድንጋዮች አመጡ። 12ንጉሡም የሰንደሉን ዕንጨት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለቤተ መንግሥቱ መደገፊያ፣ ለመዘምራኑ የመሰንቆና የበገና መሥሪያ አደረገው። ይህን ያህል ብዛት ያለው የሰንደል ዕንጨት እስከ ዛሬ ድረስ ከቶ አልመጣም፤ አልታየምም።
13ንጉሥ ሰሎሞንም ለሳባ ንግሥት ከቤተ መንግሥቱ በልግስና ከሚሰጣት ሌላ፣ የፈለገችውንና የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ከዚያም ከአጃቢዎቿ ጋራ ወደ አገሯ ተመለሰች።
የሰሎሞን ብልጽግናና ክብር
10፥14-29 ተጓ ምብ – 2ዜና 1፥14-17፤ 9፥13-28
14ለሰሎሞን በየዓመቱ የሚገባለት ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት የሚመዝን ወርቅ ነበር።#10፥14 23 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። 15ይህም ከታላላቅና ከተራ ነጋዴዎች ከሚገባው ቀረጥ፣ መላው የዐረብ ነገሥታት ከሚያስገቡትና አገረ ገዦች ከሚሰበስቡት ግብር ሌላ ነበር።
16ንጉሥ ሰሎሞን ከጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ ትላልቅ ጋሻዎችን አበጀ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ስድስት መቶ ሰቅል ጥፍጥፍ#10፥16 6.9 ኪሎ ግራም ያህል ነው። በተጨማሪም በቍጥር 29 ወርቅ ነበር። 17እንዲሁም ከጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻዎችን አበጀ፤ በእያንዳንዱ ጋሻ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት ምናን#10፥17 1.7 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ነበር። ንጉሡም ጋሻዎቹን የሊባኖስ ደን በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ አኖረ።
18ከዚያም ንጉሡ በዝኆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን ሠርቶ በንጹሕ ወርቅ ለበጠው። 19ዙፋኑ ባለስድስት ደረጃ ነው፤ በስተ ኋላውም ዐናቱ ላይ ክብ ቅርጽ ሲኖረው፣ ግራና ቀኙ ባለመደገፊያ ነው፤ መቀመጫውም ግራና ቀኙ መደገፊያ ያለው ሲሆን፣ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመዋል። 20በስድስቱም ደረጃዎች ጫፍ ላይ ግራና ቀኝ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመዋል። ይህን የመሰለ ዙፋን በማንኛውም አገር መንግሥት ተሠርቶ አያውቅም። 21ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩትም ዕቃዎች ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር ዋጋ እንደሌለው ስለሚቈጠር ከብር የተሠራ አንድም ነገር አልነበረም። 22ንጉሡ ከኪራም መርከቦች ጋራ ዐብረው በባሕር ላይ የሚጓዙ የተርሴስ የንግድ መርከቦች#10፥22 ዕብራይስጡ የተርሴስ መርከቦች ይላል። ነበሩት። እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብርና የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች ያመጡ ነበር።
23ንጉሥ ሰሎሞን በሀብትም ሆነ በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር። 24ዓለሙ ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ከሰሎሞን ጋራ መገናኘት ይፈልግ ነበር። 25በየዓመቱም የሚመጣው ሰው ሁሉ የብርና የወርቅ ዕቃ፣ ልብስ፣ የጦር መሣሪያ፣ ቅመማ ቅመም፣ ፈረስና በቅሎ ስጦታ አድርጎ ያመጣለት ነበር።
26ሰሎሞን ሠረገሎችንና#10፥26 ወይም ሠረገለኞች ተብሎ መተርጐም ይችላል። ፈረሶችን ሰበሰበ፤ እርሱም አንድ ሺሕ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች ነበሩት፤ እነርሱንም በሠረገላ ከተሞችና ንጉሡ ባለበት በኢየሩሳሌም ከተማ አኖራቸው። 27ንጉሡ በኢየሩሳሌም ብሩን እንደ ማንኛውም ድንጋይ፣ የዝግባውንም ዕንጨት ብዛት በየኰረብታው ግርጌ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው። 28የሰሎሞን ፈረሶች የመጡት ከግብጽና ከቀዌ#10፥28 ምናልባት ኪልቂያ ልትሆን ትችላለች። ሲሆን፣ ከቀዌ የገዟቸውም የንጉሡ ነጋዴዎች ነበሩ። 29ከግብጽ ያስመጧቸውም አንዱን ሠረገላ በስድስት መቶ ሰቅል#10፥29 6.9 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ብር፣ አንዱን ፈረስ በአንድ መቶ ዐምሳ ሰቅል#10፥29 1.7 ኪሎ ግራም ነው። ብር ገዝተው ነው። እነዚህንም ደግሞ ለኬጢያውያንና ለሶርያውያን ነገሥታት ሁሉ ይሸጡላቸው ነበር።
Currently Selected:
1 ነገሥት 10: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.