1 ነገሥት 1
1
አዶንያስ ለመንገሥ እንደ ፈለገ
1ንጉሥ ዳዊት እየሸመገለና ዕድሜው በጣም እየገፋ ሲሄድ፣ ልብስ ቢደራርቡለትም እንኳ ሊሞቀው አልቻለም። 2ስለዚህ አገልጋዮቹ፣ “ንጉሡን የምትንከባከብና የምታገለግል ወጣት ድንግል እንፈልግ፤ እርሷም ጌታችን ንጉሡ እንዲሞቀው በጐኑ ትተኛለች” አሉት።
3ከዚያም በመላው እስራኤል ቈንጆ ልጃገረድ ፈልገው ሱነማዪቱን አቢሳን አገኙ፤ ለንጉሡም አመጡለት። 4ልጃገረዲቱ እጅግ ቈንጆ ነበረች፤ ንጉሡንም ትንከባከበውና ታገለግለው ነበር፤ ንጉሡ ግን ከርሷ ጋራ ግንኙነት አልነበረውም።
5በዚህ ጊዜ ከአጊት የተወለደው አዶንያስ፣ “እነግሣለሁ” ብሎ ተነሣ፤ ስለዚህ ሠረገሎችንና#1፥5 ወይም ሠረገለኞች ተብሎ ሊተረጐም ይችላል። ፈረሶችን እንዲሁም ከፊት ከፊቱ የሚሄዱ ዐምሳ ሰዎችን አዘጋጀ። 6አባቱም፣ “ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?” ብሎ ገሥጾት አያውቅም ነበር፤ አዶንያስም እጅግ መልከ መልካምና የአቤሴሎም ታናሽ ወንድም ነበር።
7አዶንያስ ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋራ ተመካከረ፤ እነርሱም ድጋፋቸውን ሰጡት። 8ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅ፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ነቢዩ ናታን፣ ሳሚ፣ ሬሲና#1፥8 ወይም እና ጓደኞቹ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል። የዳዊት የክብር ዘበኞች ከአዶንያስ ጋራ አልተባበሩም።
9ከዚያም አዶንያስ በዓይንሮጌል አቅራቢያ ባለው የዞሔልት ድንጋይ አጠገብ በጎችን፣ በሬዎችንና የሠቡ ጥጆችን ሠዋ፤ ወንድሞቹን ሁሉ፣ የንጉሡን ልጆች እንዲሁም የቤተ መንግሥቱ ሹማምት የነበሩትን የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ጠራ፤ 10ይሁን እንጂ ነቢዩ ናታንንም ሆነ በናያስን፣ የክብር ዘበኞቹንም ሆነ ወንድሙን ሰሎሞንን አልጠራም።
11ከዚያም ናታን የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን እንዲህ አላት፤ “ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የአጊት ልጅ አዶንያስ መንገሡን አልሰማሽምን? 12አሁንም የራስሽንና የልጅሽን የሰሎሞንን ሕይወት እንዴት ማዳን እንደምትችዪ ልምከርሽ፤ 13ወደ ንጉሥ ዳዊት ሂጂና፣ ‘ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ “ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ ቀጥሎ ይነግሣል፤ በዙፋኔም ይቀመጣል” ብለህ ለእኔ ለአገልጋይህ አልማልህልኝም ነበር? ታዲያ አዶንያስ የነገሠው ስለ ምንድን ነው?’ በዪው፤ 14አንቺ እዚያው ሆነሽ ይህን ለንጉሥ በምትነግሪው ጊዜ እኔ እገባና ያልሽው ትክክል መሆኑን አረጋግጣለሁ።”
15ስለዚህ ቤርሳቤህ፣ ሱነማዪቱ አቢሳ በምታገለግልበት ክፍል እርጅና የተጫጫነውን ንጉሥ ለማነጋገር ሄደች። 16ቤርሳቤህም ለጥ ብላ እጅ ከነሣች በኋላ እፊቱ በጕልበቷ ተንበረከከች።
ንጉሡም፣ “ምን ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት።
17እርሷም እንዲህ አለችው፣ “ጌታዬ ሆይ፤ ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ ቀጥሎ ይነግሣል፤ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለህ አንተው ራስህ ለአገልጋይህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ምለህልኝ ነበር። 18እነሆ፤ አሁንም አዶንያስ ነግሧል፤ ንጉሥ ጌታዬ አንተ ግን ስለዚህ ነገር አታውቅም። 19እርሱ በሬዎችን፣ ኰርማዎችንና በጎችን በብዛት ሠውቷል፤ የንጉሡን ልጆች በሙሉ፣ ካህኑን አብያታርንና የሰራዊቱን አዛዥ ኢዮአብን ጠርቷል፤ አገልጋይህን ሰሎሞንን ግን አልጠራውም። 20ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ ከአንተ ቀጥሎ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ ማን መቀመጥ እንዳለበት እንድታሳውቀው የእስራኤል ዐይን ሁሉ አንተን ይመለከታል። 21አለዚያ ግን ንጉሥ ጌታዬ ከአባቶቹ ጋራ በሚያንቀላፋበት ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ወንጀለኞች እንቈጠራለን።”
22እርሷ ከንጉሡ ጋራ በመነጋገር ላይ ሳለች ነቢዩ ናታን ገባ። 23ለንጉሡም፣ “ነቢዩ ናታን መጥቷል” ብለው ነገሩት፤ እርሱም ንጉሡ ፊት ቀርቦ ለጥ ብሎ እጅ ነሣ።
24ናታንም እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ ለመሆኑ አዶንያስ ከአንተ ቀጥሎ እንደሚነግሥ፣ በዙፋንህም እንደሚቀመጥ አስታውቀሃልን? 25በዛሬው ቀን ታች ወርዶ ብዙ በሬዎች፣ ኰርማዎችና በጎች ሠውቷል፤ የንጉሡን ልጆች በሙሉ፣ የሰራዊቱን አዛዦችና ካህኑን አብያታርንም ጠርቷል። እነሆ፤ አሁን፣ ‘አዶንያስ ለዘላለም ይኑር’ እያሉ ከርሱ ጋራ በመብላትና በመጠጣት ላይ ናቸው። 26ነገር ግን እኔን አገልጋይህን፣ ካህኑን ሳዶቅን፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስንና አገልጋይህን ሰሎሞንን አልጠራም፤ 27ታዲያ ከርሱ ቀጥሎ በንጉሥ ጌታዬ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን አገልጋዮቹን ሳያሳውቅ ይህ እንዲሆን ንጉሡ ፈቅዷልን?”
ዳዊት ሰሎሞን እንዲነግሥ አደረገ
1፥28-53 ተጓ ምብ – 1ዜና 29፥21-25
28ከዚያም ንጉሥ ዳዊት፣ “ቤርሳቤህን ጥሩልኝ” አለ፤ እርሷም ንጉሡ ወዳለበት ገብታ በፊቱ ቆመች።
29ከዚያም ንጉሡ እንዲህ ሲል ማለ፤ “ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳናት ሕያው እግዚአብሔርን! 30‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ ቀጥሎ ይነግሣል፤ በእኔም ምትክ በዙፋኔ ይቀመጣል’ ብዬ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር የማልሁልሽን ዛሬ በእውነት እፈጽማለሁ።”
31ቤርሳቤህም ለጥ ብላ እጅ ከነሣች በኋላ፣ በንጉሡ ፊት ተንበርክካ፣ “ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም ይኑር!” አለች።
32ንጉሥ ዳዊትም፣ “ካህኑን ሳዶቅን፣ ነቢዩን ናታንንና የዮዳሄን ልጅ በናያስን ጥሩልኝ” አለ። እነርሱም ንጉሡ ፊት በቀረቡ ጊዜ፣ 33ንጉሡ እንዲህ አላቸው፤ “የጌታችሁን አገልጋዮች ይዛችሁ በመሄድ ልጄን ሰሎሞንን በራሴ በቅሎ ላይ አስቀምጡት፤ ወደ ግዮንም ይዛችሁት ውረዱ። 34በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን ቀብተው በእስራኤል ላይ ያንግሡት፤ ቀንደ መለከት ነፍታችሁም፣ ‘ንጉሥ ሰሎሞን ለዘላለም ይኑር!’ ብላችሁ ጩኹ። 35አጅባችሁት ወደ ላይ ውጡ፤ ከዚያም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፤ በእኔም ምትክ ይግዛ፤ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ሾሜዋለሁ።”
36የዮዳሄ ልጅ በናያስም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አሜን! የጌታዬ የንጉሡ አምላክ እግዚአብሔር ይህንኑ ያጽናው። 37እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሡ ጋራ እንደ ነበረ ሁሉ፣ ከሰሎሞንም ጋራ ይሁን፤ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሥ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርገው።”
38ስለዚህ ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ከሊታውያንና ፈሊታውያን ወርደው ሰሎሞንን በንጉሥ ዳዊት በቅሎ አስቀምጠው በማጀብ ወደ ግዮን አመጡት። 39ካህኑ ሳዶቅም የዘይቱን ቀንድ ከመገናኛው ድንኳን ወስዶ ሰሎሞንን ቀባው፤ ከዚያም ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ሕዝቡም በሙሉ፣ “ንጉሥ ሰሎሞን ለዘላለም ይኑር!” በማለት ዳር እስከ ዳር አስተጋቡ። 40ሕዝቡ ሁሉ እንቢልታ እየነፋና እጅግ እየተደሰተ አጀበው፤ ከድምፁ የተነሣም ምድሪቱ ተናወጠች።
41አዶንያስና የተጠሩት እንግዶች ሁሉ ግብዣውን በማገባደድ ላይ ሳሉ፣ ይህንኑ ሰሙ፤ ኢዮአብም የመለከቱን ድምፅ ሲሰማ፣ “ይህ በከተማዪቱ ውስጥ የሚሰማው ድምፅ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።
42ኢዮአብ ገና ተናግሮ ሳይጨርስ፣ የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን ደረሰ፤ አዶንያስም፣ “እንደ አንተ ያለ ታማኝ ሰው መልካም ዜና ሳይዝ አይመጣምና ግባ” አለው።
43ዮናታንም እንዲህ ሲል ለአዶንያስ መለሰ፣ “ነገሩ ከቶ እንዲህ አይደለም! ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አንግሦታል። 44ንጉሡ ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ከሊታውያንና ፈሊታውያን ዐብረውት እንዲሄዱ አድርጓል፤ እነርሱም በንጉሡ በቅሎ አስቀመጡት። 45ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ቀብተው አንግሠውታል። ከዚያም ደስ ብሏቸው ወጥተዋል፤ ከተማዪቱም ይህንኑ አስተጋብታለች፤ እንግዲህ የሰማችሁት ድምፅ ይኸው ነው። 46ከዚህም ሌላ ሰሎሞን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጧል። 47የመንግሥቱ ሹማምትም ወደ ጌታችን ወደ ንጉሥ ዳዊት መጥተው፣ ‘አምላክህ የሰሎሞንን ስም ከአንተ ስም የላቀ፣ ዙፋኑንም ከአንተ ዙፋን የበለጠ ያድርገው’ በማለት ባረኩት። ንጉሡም ዐልጋው ላይ ሆኖ በመስገድ፣ 48‘ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን ወራሽ ዐይኔ እንዲያይ የፈቀደ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፣ ምስጋና ይድረሰው’ አለ።”
49በዚህም አዶንያስና የጠራቸው እንግዶች በሙሉ ደንግጠው ተነሡ፤ በየአቅጣጫውም ተበታተኑ። 50አዶንያስ ግን ሰሎሞንን በመፍራት ሄዶ፣ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ። 51ከዚያም፣ ለሰሎሞን፣ “አዶንያስ እነሆ፣ ንጉሥ ሰሎሞንን በመፍራት የመሠዊያውን ቀንድ ይዞ ተማጥኗል፤ እርሱም፣ ‘ባሪያውን በሰይፍ እንዳይገድለው ንጉሡ ሰሎሞን ዛሬውኑ ይማልልኝ’ ብሏል” ብለው ነገሩት።
52ሰሎሞንም፣ “አካሄዱን ካሳመረ ከራስ ጠጕሩ አንዲቱ እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም፤ ጥፋት ከተገኘበት ግን ይሞታል” ሲል መለሰ። 53ከዚያም ንጉሥ ሰሎሞን ሰዎች ልኮ ከመሠዊያው ላይ አወረዱት። አዶንያስም መጥቶ ለንጉሥ ሰሎሞን አጐንብሶ እጅ ነሣ፤ ሰሎሞንም፣ “በል ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።
Currently Selected:
1 ነገሥት 1: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.