1 ቆሮንቶስ 7:1-24

1 ቆሮንቶስ 7:1-24 NASV

ስለ ጻፋችሁልኝ ጕዳይ፣ ሰው ወደ ሴት ባይደርስ መልካም ነው፤ ነገር ግን ከዝሙት ለመጠበቅ፣ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዷም ሴት የራሷ ባል ይኑራት። ባል ለሚስቱ የሚገባትን ሁሉ ያድርግላት፤ ሚስትም ለባሏ እንዲሁ። ሚስት በራሷ አካል ላይ ሥልጣን የላትም፤ ባሏ እንጂ። እንዲሁም ባል በራሱ አካል ላይ ሥልጣን የለውም፤ ሚስቱ እንጂ። በጸሎት ለመትጋት ተስማምታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በቀር፣ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ባለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ እንደ ገና ዐብራችሁ ሁኑ። ይህን የምለው ግን እንደ ትእዛዝ ሳይሆን እንደ ምክር ነው። ሰው ሁሉ እንደ እኔ ቢሆን ምኞቴ ነው። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ከእግዚአብሔር የተቀበለው የራሱ የሆነ ስጦታ አለው፤ አንዱ አንድ ዐይነት ስጦታ ሲኖረው፣ ሌላው ደግሞ ሌላ ዐይነት ስጦታ አለው። ላላገቡና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ግን እንዲህ እላለሁ፤ ሳያገቡ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው። ነገር ግን ራሳቸውን መግዛት ካልቻሉ ያግቡ፤ በምኞት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና። ላገቡት ይህን ትእዛዝ እሰጣለሁ፤ ይህም ትእዛዝ የጌታ እንጂ የእኔ አይደለም። ሚስት ከባሏ አትለያይ፤ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር፤ አለዚያ ከባሏ ጋራ ትታረቅ፤ ባልም ሚስቱን አይፍታት። ለሌሎች ደግሞ እንዲህ እላለሁ፤ ይህንም የምለው እኔ እንጂ ጌታ አይደለም። ያላመነች ሚስት ያለው ወንድም ቢኖርና ሚስቱ ዐብራው ለመኖር የምትፈቅድ ከሆነ፣ ሊፈታት አይገባውም። ያላመነ ባል ያላት ሴት ብትኖርና እርሱም ዐብሯት ለመኖር የሚፈቅድ ከሆነ፣ ልትፈታው አይገባትም። ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሷልና፤ ያላመነችም ሚስት በሚያምን ባሏ ተቀድሳለች፤ አለዚያማ ልጆቻችሁ ርኩሳን በሆኑ ነበር፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው። ነገር ግን የማያምነው ወገን መለየት ከፈለገ ይለይ፤ አንድ ወንድም ወይም እኅት በዚህ ሁኔታ የታሰሩ አይደሉም፤ እግዚአብሔር የጠራን በሰላም እንድንኖር ነው። አንቺ ሴት፤ ባልሽን ታድኚው እንደ ሆነ ምን ታውቂያለሽ? ወይስ አንተ ሰው፤ ሚስትህን ታድናት እንደ ሆነ ምን ታውቃለህ? ብቻ እያንዳንዱ ሰው ጌታ እንደ ወሰነለት፣ እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው በዚያው ይመላለስ። በአብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ የምንደነግገው ይህንኑ ነው። አንድ ሰው ተገርዞ ሳለ ቢጠራ፣ እንዳልተገረዘ ሰው አይሁን፤ ሳይገረዝም ተጠርቶ ከሆነ አይገረዝ። መገረዝም ሆነ አለመገረዝ አይጠቅምም፤ ዋናው ነገር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸሙ ነው። እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ሁኔታ ጸንቶ ይኑር። በተጠራህ ጊዜ ባሪያ ነበርህን? በዚህ አትጨነቅ፤ ነጻነትህን ማግኘት ከቻልህ ግን ነጻነትህን ተቀበል። ምክንያቱም ባሪያ ሆኖ ሳለ በጌታ የተጠራ፣ የጌታ ነጻ ሰው ነው፤ እንዲሁም ሲጠራ ነጻ የነበረ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው። በዋጋ ተገዝታችኋል፤ ስለዚህ የሰው ባሮች አትሁኑ። ወንድሞች ሆይ፤ እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ሁኔታ ከእግዚአብሔር ጋራ ጸንቶ ይኑር።