1 ቆሮንቶስ 6
6
መካሰስ በክርስቲያኖች መካከል
1ከመካከላችሁ አንድ ሰው ከሌላው ጋራ ሙግት ቢኖረው፣ ጕዳዩን በቅዱሳን ፊት በማቅረብ ፈንታ እንዴት ደፍሮ በዐመፀኞች ፊት ለመፋረድ ያቀርባል? 2ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? በዓለም ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፣ እንግዲያው፣ በትንሹ ነገር ላይ ለመፍረድ አትበቁምን? 3በምድራዊ ሕይወት ጕዳይ ቀርቶ፣ በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን? 4እንግዲህ እንዲህ ያለ ጕዳይ ሲያጋጥማችሁ፣ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጅ አድርጋችሁ ሹሟ#6፥4 ወይም በቤተ ክርስቲያን የተናቁ ሰዎችን ፈራጅ አድርጋችሁ ትሾማላችሁ?! 5ይህንም የምለው ላሳፍራችሁ ብዬ ነው። ለመሆኑ በወንድሞች መካከል ለመፍረድ የሚበቃ ጠቢብ ሰው በመካከላችሁ የለምን? 6ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ለመክሰስ ፍርድ ቤት ይሄዳል፤ ያውም በማያምኑ ሰዎች ፊት!
7እንግዲህ በመካከላችሁ መካሰስ መኖሩ ራሱ ውድቀታችሁን ያሳያል። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? 8እናንተ ግን ራሳችሁ ትበድላላችሁ፤ ታታልላላችሁም፤ ያውም እኮ ወንድሞቻችሁን። 9ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ወንደቃዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ 10ወይም ሌቦች፣ ስግብግቦች፣ ሰካራሞች፣ ተሳዳቢዎችና ቀማኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። 11ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ እንደዚህ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል።
ዝሙት
12“ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤” ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር አይጠቅምም፤ “ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤” ይሁን እንጂ ምንም ነገር በእኔ ላይ አይሠለጥንም። 13ደግሞም፣ “ምግብ ለሆድ ነው፤ ሆድም ለምግብ ነው፤” እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ያጠፋቸዋል። ሰውነት ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሰውነት ነው። 14እግዚአብሔር ጌታን ከሙታን እንዳስነሣው፣ እኛንም ደግሞ በኀይሉ ከሙታን ያስነሣናል። 15ሰውነታችሁ የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? ታዲያ፣ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ ከዝሙት ዐዳሪ ብልቶች ጋራ አንድ ላድርገውን? ከቶ አይሆንም! 16ወይስ ከዝሙት ዐዳሪ ጋራ የሚተባበር ሰው ከርሷ ጋራ አንድ ሥጋ እንደሚሆን አታውቁምን? “ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ”#6፥16 ዘፍ 2፥24 ተብሏልና። 17ነገር ግን ከጌታ ጋራ የሚተባበር ከርሱ ጋራ አንድ መንፈስ ይሆናል።
18ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚሠራው ኀጢአት ሁሉ ከአካሉ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚፈጽም ግን በገዛ አካሉ ላይ ኀጢአት ይሠራል። 19ለመሆኑ፣ ሰውነታችሁ በውስጣችሁ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ይህም መንፈስ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት ነው። እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም፤ 20በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።
Currently Selected:
1 ቆሮንቶስ 6: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.