አሁን ደግሞ ለቅዱሳን ስለሚደረገው ገንዘብ ማሰባሰብ፤ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት በሰጠሁት ትእዛዝ መሠረት አድርጉ። ገንዘብ ማሰባሰብ የሚደረገው እኔ በምመጣበት ጊዜ እንዳይሆን፣ ከእናንተ እያንዳንዱ እንደ ገቢው መጠን በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን እየለየ ያስቀምጥ። በምመጣበት ጊዜ እናንተ ለመረጣችኋቸው ሰዎች የመሸኛ ደብዳቤ ሰጥቼ ስጦታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያደርሱ እልካቸዋለሁ። የእኔ መሄድ የሚያስፈልግ ከሆነ አብረውኝ ይሄዳሉ። በመቄዶንያ በኩል ማለፌ ስለማይቀር፣ መቄዶንያ ከደረስሁ በኋላ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ በጕዞዬ እንድትረዱኝ፣ እናንተ ዘንድ እቈይ ይሆናል፤ ምናልባትም ክረምቱን ከእናንተ ጋር እሰነብት ይሆናል። አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጐበኛችሁ አልፈልግም፤ ጌታ ቢፈቅድ ረዘም ላለ ጊዜ እናንተ ዘንድ ለመሰንበት ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን እስከ በዓለ አምሳ በኤፌሶን እቈያለሁ፤ ምክንያቱም ታላቅ የሥራ በር ተከፍቶልኛል፤ ብዙ ተቃዋሚዎችም አሉብኝ። ጢሞቴዎስ ወደ እናንተ ከመጣ፣ አብሯችሁ ያለ ፍርሀት እንዲቀመጥ አድርጉ፤ እርሱም እንደ እኔ የጌታን ሥራ የሚሠራ ነውና። ስለዚህ ማንም አይናቀው፤ በሰላም ወደ እኔ እንዲመለስ ርዱት፤ መመለሱንም ከወንድሞች ጋር እየጠበቅን ነው። ስለ ወንድማችን ስለ አጵሎስ ደግሞ፣ ከወንድሞች ጋር ወደ እናንተ እንዲመጣ አጥብቄ ለምኜው ነበር፤ እርሱ ግን አሁን ለመምጣት አልፈለገም፤ ሲመቸው ግን ይመጣል። ንቁ፤ በእምነት ጽኑ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ፤ የምታደርጉትን ሁሉ በፍቅር አድርጉ። የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች በአካይያ የመጀመሪያዎቹ አማኞች እንደ ሆኑና ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደ ሰጡ ታውቃላችሁ። ወንድሞች ሆይ፤ ይህን እለምናችኋለሁ፤ እንደ እነርሱ ላሉትና ከእነርሱም ጋር በአገልግሎት ለሚደክሙ ሁሉ ታዘዙ። እስጢፋኖስ፣ ፈርዶናጥስና አካይቆስ በመምጣታቸው ደስ ብሎኛል፤ ምክንያቱም እናንተ እዚህ ባለመኖራችሁ የጐደለኝን አሟልተዋል፤ የእኔንም የእናንተንም መንፈስ አሳርፈዋልና። ስለዚህ እንደነዚህ ያሉት ሰዎች መታወቅ ይገባቸዋል። በእስያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። አቂላና ጵርስቅላ፣ በቤታቸውም ያለችው ቤተ ክርስቲያን የከበረ ሰላምታ በጌታ ያቀርቡላችኋል። ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። እርስ በርሳችሁ በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ የጻፍሁላችሁ እኔ ጳውሎስ ነኝ። ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታ ሆይ፤ ና! የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። ፍቅሬ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሁላችሁ ጋር ነው፤ አሜን።
1 ቆሮንቶስ 16 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ቆሮንቶስ 16
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ቆሮንቶስ 16:1-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos