የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ዜና መዋዕል 22

22
1ከዚያም ዳዊት፣ “ከእንግዲህ የእግዚአብሔር አምላክ ቤት በዚህ ይሆናል፤ እንዲሁም ስለ እስራኤል የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ በዚሁ ይቆማል” አለ።
ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት
2ስለዚህ ዳዊት በእስራኤል የሚኖሩ መጻተኞች እንዲሰበሰቡ አዘዘ፤ ከመካከላቸውም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚሠራበትን ጥርብ ድንጋይ እንዲያዘጋጁ ጠራቢዎችን መደበ። 3ለቅጥር በሮቹ ምስማርና ማጠፊያ የሚሆን ብዙ ብረትና ከብዛቱ የተነሣ ሊመዘን የማይቻል ናስ አዘጋጀ። 4እንዲሁም ሲዶናውያንና ጢሮሳውያን በብዛት አምጥተውለት ስለ ነበር፣ ስፍር ቍጥር የሌለው የዝግባ ዕንጨት አሰናዳ።
5ዳዊትም፣ “ልጄ ሰሎሞን ወጣት ነው፤ ልምዱም የለውም፤ ለእግዚአብሔር የሚሠራው ቤተ መቅደስ ደግሞ እጅግ የሚያምር፣ በአሕዛብም ሁሉ ዘንድ ዝናው የተሰማና እጅግ የተዋበ መሆን አለበት፤ ስለዚህ ሁሉንም እኔ አዘጋጃለሁ” አለ። እንዳለውም ዳዊት ከመሞቱ በፊት በብዛት አዘጋጀ።
6ከዚያም ልጁን ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት እንዲሠራ አዘዘው።
7ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “ልጄ ሆይ፤ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ለመሥራት በልቤ ዐስብ ነበር፤ 8ነገር ግን ከእግዚአብሔር እንዲህ የሚል ቃል መጣልኝ፤ ‘አንተ ብዙ ደም አፍስሰሃል፤ ብዙ ጦርነትም አድርገሃል፤ በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም ያፈሰስህ ስለሆነ፣ አንተ ለስሜ ቤት አትሠራልኝም፤ 9ነገር ግን የሰላምና የዕረፍት ሰው የሆነ ልጅ ትወልዳለህ፤ በየአቅጣጫው ካሉ ጠላቶቹ አሳርፈዋለሁ፤ ስሙም ሰሎሞን ይባላል። በዘመኑም ለእስራኤል ሰላምንና ጸጥታን እሰጣለሁ። 10ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ እርሱ ነው። እርሱ ልጅ ይሆነኛል፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ። ዙፋኑንም በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።’
11“አሁንም ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ እንድትፈጽመው በተናገረውም መሠረት፣ ተሳክቶልህ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ያብቃህ። 12በእስራኤል ላይ አለቃ ባደረገህ ጊዜ፣ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትፈጽም ዘንድ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ። 13እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለእስራኤል የሰጠውን ሕጉንና ሥርዐቱን ተጠንቅቀህ ብትጠብቅ ይሳካልሃል፤ አይዞህ ጠንክር፤ በርታ፤ ተስፋም አትቍረጥ።
14ለእግዚአብሔር ቤት እንዲሆንም አንድ ሺሕ መክሊት#22፥14 3,450 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው ወርቅ፣ አንድ ሚሊዮን መክሊት#22፥14 34,500 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው ብር፣ ከብዛቱ የተነሣ ሊመዘን የማይቻል ናስና ብረት ለማዘጋጀት በተቻለኝ ሁሉ ጥሬአለሁ፤ በተረፈ አንተ ጨምርበት። 15ድንጋይ ጠራቢዎች፣ ግንበኞች፣ ዐናጢዎች የሆኑ ብዙ ሠራተኞች፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሙያ የተጠበቡ ሰዎች አሉህ፤ 16እነዚህም ቍጥራቸው እጅግ የበዛ የወርቅ፣ የብር፣ የናስና የብረት ሠራተኞች ናቸው። በል ሥራህን ጀምር፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን።”
17ከዚያም ዳዊት የእስራኤል መሪዎች ሁሉ ልጁን ሰሎሞንን እንዲረዱት አዘዘ፤ 18እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር አምላካችሁ እስካሁን ከእናንተ ጋር አይደለምን? በየአቅጣጫውስ ዕረፍትን ሰጥቷችሁ የለምን? የምድሪቱን ነዋሪዎች በእጄ አሳልፎ ሰጥቶኛል፤ ምድሪቱም ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ ተገዝታለች። 19አሁንም እግዚአብሔር አምላካችሁን ለመፈለግ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ሰብስቡ። የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦትና ንዋያተ ቅድሳቱን ለእግዚአብሔር ስም ወደሚሠራው ቤተ መቅደስ አምጥታችሁ የአምላክን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ