ቀና ብዬ ስመለከት ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ከሰሜን በኩል ሲመጣ አየሁ፤ ከግዙፍ ደመና የመብረቅ ብልጭታ ይታይ ነበር፤ በዙሪያው ያለውም ሰማይ ቀላ፤ መብረቁ በሚበርቅበትም ስፍራ አንዳች ነገር እንደ ነሐስ አበራ። በዐውሎ ነፋሱም መካከል የሰው መልክ ያላቸው አራት ሕያዋን ፍጥረቶች አየሁ፤ እያንዳንዱም ፍጥረት አራት አራት ፊትና አራት አራት ክንፍ ነበሩት። እግራቸው ቀጥ ያለ ሲሆን፥ ውስጥ እግራቸው እንደ ኰርማ ሰኮና ነበር፤ መልካቸውም እንደ ተወለወለ ነሐስ ያበራ ነበር፤ ከአራቱ ፊቶቻቸውና ከአራቱ ክንፎቻቸው ሌላ እያንዳንዳቸው ከክንፎቻቸው ግርጌ አራት የሰው ዐይነት እጆች ነበሩአቸው። የእያንዳንዱ ፍጥረት ሁለት ክንፎች ግራና ቀኝ ተዘርግተው ጫፎቻቸው ይነካካሉ፤ ስለዚህ ሰውነታቸው ወዲያና ወዲህ ሳይል በኅብረት ይንቀሳቀሱ ነበር።